!July 19, 2013
ከሥርጉተ ሥላሴ
ወይ ጉድ ዛሬ ደግሞ ተነሳብኝ። እንቢኝ በይ ይለኛል። አሻም በይ ይለኛል። አይሆንም በይ ይለኛል። በቃን በይ ይለኛል። ይለኛል – ይለኛል። ያፋጥጠኛል። ሲያሰኛው ይገፈትረኛል። ሲያሻው ያሸኛል። እኮ! እኔም ፈቅጄለት ይሁንልህ ብዬዋለሁ። እንዳሻህም አልኩት እንዴ! ነፃነት የሚሉት እንዲህ ዛሬ ከእኔ ለእኔ ካልተጀመረ መቼ ….
እህ! ቀጠሮ ለመቼ? ለነገ አይሆንም። ዛሬ … ይኸው ዛሬ …. እኔ ለእኔ ሙሉውን ነፃነት በሸማ አጎናጽፌ፤ በካባ አሽሞንሙኜ በሙሉ ወርድ አንቆጥቁጭ፤ ነጋሪት ጉሰማ … እንዲያም ሲል ቀረርቶ … ፉከራ …. አቤት ስንት ተጓዝኩ መሰላችሁ ….
ሥነ – ጥበብ ህይወት ነው። ሥነ – ጥበብ እውቀት ነው። ሥነ – ጥበብ ኑሮ ነው። ሥነ ጥበብ – ሥጦታ ነው …. ወዘተ ወዘተ …. በዚህ እንስማማለን። ይመስለኛል። ስለምን ይመስለኛል አልኩ ነው እንጂ …. እርግጡ ከነፍሬው ይገለጥ …. ብያለሁ። ብዙ ቀርቶኛል ስለ ሥነ ጥበብ ከሁሉም በላይ ሥነ ጥበብ ፍትህና እውነት ነው። የሚጨበጥ የሚዳሰስ …
የሥነ ጥብብ ሃብት ከማህበረሰቡ ጓዳ ይታፋሳል። ታዲያ መታፈስ የሚችለው እውነት ሲሆን፤ ሚዛኑን ሲጠብቅ ብቻ ይሆናል። ለመሆኑ ለ30ኛው የኢትዮጵውያን የስፖርት ፌስቲባል የመዝጊያ ሙዚቃ የኢትዮጵውያን የጋራ ዝማሬ የሆነውን አርቲስት አስቴር ስታቀነቅነው አብራችሁ ዘመራችሁ ይሆን? ከመቀመጫችሁ ንቅንቅ አደረጋችሁ ይሆን? እንዲያው እንዴትና እንዴት አደረጋችሁ …. እኔ እህታችሁ ወይ አብሮ መዘመር … ቃናው ነው የጠፋብኝ። ያን ያህል ከመቀመጫዬ አስነስቶ በጩኽት የማዜመው አልነበረም …. መራር ነበር …
ዋሽንግተን ዲሲ አልነበርኩም። ግን ቤቴ ውስጥ በማናቸውም የነፃነት ጉዳዮች ላይ በተመስጦ ነው የምታደመው። በቂ ጊዜ ለማንበብ፤ ለማድመጥ፤ ለማዬት …. እሰጣለሁ። ለእኔ ት/ቤቴ መዝናኛ ተቋሜ ነውና …. የሆነ ሆኖ የእሷ የድምጽ ቅላጼ ያልመረከኝ፤ ያላቆነጠነጠኝ … ስለምን ይመስላችኋል? እሷ በእኔ ውስጥ ስለሌለች ነው ….
የአንድ የጥበብ ሥራ መለካት፤ መሰፈር፤ መመዘን ያለበት በእውነት በውስጥ መሆን አለበት። እሷና ሃቅ ተራርቀው የኖሩ ናቸው። ለነገሩ የብሄራዊ ዜማችን ሃብትነቱ የእሷም አይደለም። ባይሆንም ግን እጅግ የምወደው ስለነበር መታደም ነበረብኝ። አዎና እንብኝ አለ፤ አሻም አለ፤ አሻፈረኝ አለ መንፈሴ። እኔም ጎሽ ብዬ አስጎንብሼ መረቅኩት። ይገባዋል አይደል?!
ለእኔ አርቲስት ሻንበልና አርቲስት አስቴር ቢቀርቡ የሲኒሪቲ ጉዳይ ቢነሳ አርቲስት ሻንበል ይበልጥብኛል። አርቲስት መሃሙድና አርቲስት ቴዲ ቢወዳደሩም አርቲስት ቴዲ ይበልጥብኛል። መለኪያዬ እውነትና ከዛም ባለፈ የኢትዮጵያን ዕንባ መጋራት ስለሆነ መስፈርቴ። ነፃነት አለ …. ነፃነቱ ግን ሥነ ምግባር አለው። ከሥነ ምግባሩ ያፈነገጠ ጸጋና ክህሎት ባይፈጠር ይሻላዋል። …. አድናቂውም አክባሪውም አይደለሁም። ለዚህ ይቅርታ ማንንም አልጠይቅም። አሁን አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬና አርቲስ አለምጸሐይ ወዳጆ በእንዴት ያለ መስፈርት ነው ሊመጣጠኑስ ሊወዳደሩስ ሚችሉት ….?
የህዝብ ፍቅር ማለት እኮ ኑሮውን መኖር ማለት ነው። …. ሳይኖሩት እንዴት ሃብት ሊሆኑ ይችላሉ። ከገዳይ ጋር ለሚጨፍሩ፤ ከጨካኝ ጋር ለታደሙ እንዴት …. ተብሎ። እንብኝ ብያለሁ። አሁን ፍቅር አዲስ ለእኔ ምንድን ናት? አብሮ አደጌም ናት። ወጣት እያለች የእህቴም ጓደኛ ነበረች። ነገር ግን ሆዱ ዘመዴ ስለሆነች አሁን ለ እኔም ሆነ ለእህቴ ምንም ናት እሺ!
እንዴት ነው ነገሩ ማንተርተሪያ ሰፌድ፤ መለያም ወንፊት መለኪያም ሚዛን ይኑረን እንጂ። ይህ ካልኖረ አማረብን ብለው ዕንባን እደረገጡ ሊቀጥሉ ነው። በሌላ በኩል በሰብዕዊ መብት ረገጣ ዙሪያ ግልጽና ቀጥተኛ አቋም የያዙትን የነፃነት ትግሉን አርቲስት ቤተሰቦችንም ሞራል መንካት ነው። እነኝህ ለሰብዕዊ ፍጡር ፍጹም ደንታ የሌላቸው አርቲስቶች እኮ እንዲህ ከከበከብናቸው ዕዳው አራጣ ባራጣ ነው። በመጨረሻም ምህረት ሳይጠይቁ ያልፋሉ። ይህ ለትውልዱ በደል ነው …. ቀጣዩንም መስመር ለማስያዝ ይቸግራል …. መቀጠት መቆንጠጥ አለበት። መታረቅ አለበት፤ መልክ መያዝ አለበት።
እና የእኔ መንፈስ በወያኔ ደጋፊ አርቲስቶች ላይ የሸፈተ፤ ጫካ የገባ፤ አሻፈረኝ ያለ ነው …. የእናንተስ? የሚገርማችሁ እንዲህ በአጋጣሚ ከመልካም ነገሮች ጋር ተቀላቅሎ ሲቀርብ እንኳን የእኔ አይመስለኝም። ከእነሱ ይልቅ የጀርመንኛው ሽላገ ሙዚቅ ይሻለኛል። ይስርቀኛልም። … መወደድ ማፍቀር እኮ ከማንነት አክብሮት ማህጸን ውስጥ ሊመነጭ ይገባዋል። ማንነትን፤ እኛነትን ለሚያጠፋ ፖሊሲ ለሚያረገርጉ አርቲስቶች እኔ እንብኝ እላለሁ ….። እርግጥ ነው ጸጥ ብለው ገፍተው ሳይደግፉ ሳይቃወሙም እንጃራችን በልተን እንደር የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህን ነጠል አርገን አስታምሙ ብንባል ይሁን ልንል እንችላለን። ነገር ግን ለወያኔ ካድሬ አርቲስቶች ግን በቃችሁን ማለት ይገባናል።
በሌላ በኩል ሥነ -ጥበብ ቢያንስ ለሰብዕዊ መብት ጥብቅና መቆም አለበት። እነዛን ካህዲዎች ስናከብር የአርቲስት ታማኝ ቦታ የት ሊሆን ነው? የአርቲሰት ሻንበል ቦታ የት ሊሆን ነው? የመራኂት አርቲስት አለምጸሐይ ወዳጆ ቦታ የት ላይ ልንመድበው ነው? በእስር ቤት የማቀቀው የቴዲ ቦታ የት ሊሆን ነው? የነፃነት ትግሉ ሚዲያዎች፤ ማህበራዊ ድህረ ገፆች የመወያያ መድረኮች ሁሉ ግልጽና ቀጥተኛ አቋም ይዘው ወገንተኝነታቸውን በተግባር ሊያሳዩን ይገባል።
እኔ ትውፊት ልለው የምችለው የዕንባን ቤተኛነትን ነው ከዚህ ያፈነገጠ … ውኃ ሲሄድበት የከረመ አለት ነው …. ለእኔ። ትልቋ እናት እማማ ኢትዮጵያን እኮ በወያኔ ጦርነት ታውጆባታል። … በሁለመናዋ ጠፍ እንድትሆን ነው ወያኔ ተግቶ እዬሰራ ያለው። ለዚህ አጋፋሪና ግብረ አበር ደግሞ ምህረት መስጠት አይገባም። አብሶ የኛ በምንላቸው ሚዲያዎችም ልንደንቁር አይገባም …. የምን ዝም … የምን ማዝገም ….
በእውነቱ በዕንባ ላይ የሚቀልድ፤ ቧልት የሚሰራ የሥነ ጥበብ ምርት ጣዕም የለሽ ነው። የነጠፈ ነው። ለዛ ቢስ ነው።
እግዚአብሄር አምላክ ሥነ – ጥበብን መርቆ ሲፈጥርልን ለመልካም ነገር ልንጠቀምበት እንጂ መበቀያ ወይንም መቅጫ ልናደርገው አይደለም። በህዝብ ደም ላይ ልንዘፍንበት ወይንም ልንጨፍርበት አይደለም።
ሥነ – ጥበብ ልዩ ተፈጥሮው የሚገለጠው በበጎና በከበሩ ሰብዕዊ ሥነ – ምግባሮች ነው። ይህ ነው ስጦታችን። ከዚህ ካፈነገጠ የእኛ አይደለም። … እባካችሁ አናስተውል። ሥነ – ጥበብ የአደራ ቃል ሽልማት ነው። ኪዳኑና ያመረተ ቃላ አባይ ነው። ይህን ማስተናገድ ደግሞ በዳይነት ነው። በዳይነቱ የማንነት ጠላትነት ከሆነ በአደራ ቃል ኪዳን በይነት ሁላችንም ተጠያቂ ነን እና ወንጀለኛ እንሆናለን። እባካችሁን ፈቅደን ወንጀለኝነትን አናስተናገድ። አመሰግናችኋላሁ። እውዳችኋለሁም።
ትውልዳዊ ድርሻችን በህብረትና በአንድነት እንወጣ!
እግዚአብሄር እኛን ስለ ሰጠን እንመስግነው!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
No comments:
Post a Comment