Wednesday, 6 February 2013

እኛ ስለ ሰላም እንዘምራለን፤ መንግስት ግን ዛሬም ስለ ሽብር ይናገራል


‹‹ፊልሙ›› ላነሳቸው ሃሳቦች ምላሽ የሚሰጥ የድምጽ ማብራሪያ ነገ እንለቃለን
ዛሬ የመሪዎቻችንን ጉዳይ በሚያየው አራተኛ ወንጀል ችሎት እግድ ተሰጥቶበት የነበረው ‹‹ፊልም›› በሕግ ወጥ መንገድ በኢቴቪ ተላልፏል፡፡ ‹‹ፊልሙ›› እንደለመደው ላለፈው አንድ አመት መንግስት ሲያደረግ የነበረውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ ሰላማዊ ትግል እና ተመራጭ የኮሚቴ አባላትን በሽብርተኝነት እና አክራሪነት የመወንጀል አባዜ በስፋት ሲያራምድ ነበር፡፡ ‹‹ፊልሙ›› ደጋግሞ የሙስሊሙን ማኅብረሰብ ጥያቄና የትግሉን መሪዎች ሽብርተኞች፣ የብዛ ሃይማኖቶችና ብሄሮች በሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሚሹ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላም ለማናጋት ተልእኮ የተሰጣቸው፣ ለዚህም ከውጪ ስልጠናዎችን ወስደዋል እና ሌሎችንም ሀረጎች በመጠቀም ሲወነጅላቸው አምሽቷል፡፡ የህግ የበላይነት ምሶሶ የሚባለው የተጠርጣሪዎችን ከፍርድ ውሳኔ በፊት ነጻ ሆኖ የመገመት (Presumption of innocence) መብትም ዛሬ በግልጽ ሲጣስ ተመልክተናል፡፡

እኛ ስለ ሰላም እንዘምራለን፤ መንግስት ግን ዛሬም ስለ ሽብር ይናገራል ‹‹ተጠርጣሪ አሸባሪ›› የሚል የለበጣ ሀረግ በመጠቀም የመሪዎቻችን ሕገ መንግስታዊ፤ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 20/3 ‹‹በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር፣ በምስክርነት እንዲቀርቡም ያለመገደድ መብት አላቸው፡፡›› የሚለውን አንቀጽ በመጣስ ጣቢያው ለሕግ ተገዢ እንዳልሆነ ምስክርነቱን በአደባባይ ሰጥቷል፡፡ የፍ/ቤቱንም እግድ እንዲሁ ያለ ከልካይ ጥሷል፡፡ በ‹‹ፊልሙ›› ከመንግስት በማይጠበቅ መልኩ ካሜራ በድብቅ በማስቀመጥ የሚፈልጉትን ቃላት መልቀም ያሳፍራል፡፡ ሰዎች የማይሹትን ነገር በግድ እንዲናዘዙ ማስገድ የህግ የበላይነትን ይንዳል፡፡

 በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ ንግግሮችን እየቆረጡና እየቀጠሉ (ያውም በቀሽም ቆርጦ ቀጣዮች) የተለየ መልእክት ለማስተላለፍ መሞከርም ከአንድ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ማየት በጣም ያሳዝነናል፡፡ ኮሚቴዎቻችን ትላንትም ዛሬም ነገም የምናምናቸው ስለምናምናቸውም ፈርመን ውክልና የሰጠናቸው በመሆኑ መቼም ለእነሱ ያለን ታማኝነትና ክብር አይሸረሸርም፡፡ እንደዛሬው በመሪዎቻችን ላይ የሚሰራ ተራ ፕሮፖጋንዳ ፍጻሜው ውደቀት እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡

በ‹‹ፊልሙ›› ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሳቸው የመብት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸው በስፋት ሲራገብ ነበር፤ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአገራችን በነጻነትና በተድላ እየኖርንም እንደሆነ ተነግሮናል:: ከዛሬ አንድ አመት በፊት በአወሊያ እና በመላው አገሪቱ ከሚገኙ ሙስሊሞች የቀረቡ ሦስት መሰረታዊ የእምነት ጥያቄዎችን በተወካዮቻችን አማካኝነት ለመንግስት አቅርበን ነበር፡፡ ሶስቱም ጥያቄዎች ዛሬም ምላሽ አላገኙም፡፡

 የመጅሊስ አመራርን ምርጫ መንግስት በሚፈልገው መልኩ ብቻ ለማካሄድ ስለ ፈለገ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከምርጫው ራሱን አገለለ፡፡ ምርጫውም ቅርጫ ሆኖ በጥቂት ግለሰቦች አስገቢ አስወጪነት ተካሄደ፡፡ በዚህ አይነት ድራማም ሙስሊሙ ሌላ መሪ በእጅ አዙር በመንግስት ተሾመለት፡፡ የአህባሽ አስተሳሰብ በግድ አይጫንብን ሲባል የተነሳው ሁለተኛ ጥያቄም ምላሽ ሊያገኝ ቀርቶ መንግስታዊ እስልምናን እንከተላለን ለሚሉ ጥቂት ካድሬ ኢማሞ አሳልፎ በመስጠት ሙስሊሙ ከራሱ መስጊድ ተገፍቶ እየወጣ ይገኛል፡፡ ባለፈው ወር ብቻ በመላዋ አገሪቱ ከ12 በላይ የመስጊድ ኢማሞችና የሰላት ጥሪ አድራጊዎች ከስራቸው በሀይል ተነስተው መንግስታዊ ኢማሞች በፖሊስ በመታገዝ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡

 አወሊያ ተቋም ከመጅሊስ እጅ ወጥቶ በነጻ ቦርድ ይተዳደር የሚለው ጥያቄ ዛሬም ምላሽ ሳያገኝ አሁንም ተቋሙ በመጅሊስ አመራር እጅ ውስጥ ይገኛል፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ መንግስት ምጸት ያወራል፡፡ ጥያቄውን መልሻለሁ ብሎ ሕዝብ ላይ ብሄራዊ ፌዝ ያሰማል፡፡

‹‹ፊልሙ›› ሙስሊሞች ዛሬ በኢትዮጵያ ነጻነታቸው ተጠብቆ እየኖሩ ነው ብሎ ነግሮናል፡፡ እስቲ እውነት ነው የሚል እጁን ያውጣ፡፡ ግን የዚህ ሀሳብ ምጸቱ የሚጀምረው የሙስሊሙን ህብረተሰብ መሪዎች በእስር እና ቶርች እያሰቃየ በሚያናዝ ፊልም ላይ መገለጹ ነው፡፡ ዛሬ በመላው አገሪቱ ሙስሊም መሆን ወንጀል ነው የተባለ ይመስል፤ ሙስሊሞች ለሰላት መስጊድ ሄደው በሰላም የማይመለሱበት ሁኔታ እያየን፣ የመብት ጥያቄን ያቀረቡ ሺዎች ተደብድበው ከፊሎችም ተገድለው እየተመለከትን፤ ሙስሊሞች በነጻነት እየኖሩ ነው ተብለናል፡፡

ሙስሊም ሴቶች መከናነቢያ ማድረግ ባልተከለከሉበት አገር የምን ጭቆና?ም ተብለን ተጠይቀናል፡፡ ዛሬ ይህ ‹‹ፊልም›› እየታየ ባለበት ሰዓት ግን ጥቂት በማይባሉ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች በመከናነቢያቸው ምክንያት፣ በእምነታቸው እና ጸሎት በማድረሳቸው ሳቢያ እየተገፉ እየወጡ ነው፡፡ ብዙ ሙስሊሞች ደህንነት እየተሰማቸው አይደለም፡፡ የሃይማኖት ነጻነት እንደቀልድ መገፈፈ፣ ወደ እስር ቤትም መወርወር ሙስሊሙ ላይ አይንን ከድኖ ከመግለጥ የበለጠ ቀላል ኖኗል፡፡ ግን ‹‹ፊልሙ›› ነጻነት አለ ይለናል፡፡

በአንዋር መስጊድ እና በሌሎችም አካባቢዎች ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› እያለ መፈክር የሚያሰማን ሰላማዊ ህዝብ እና የሶማሊያ ታጣቂዎችን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው ብሎ ማቅረብም መንግስት ለህዝበ ሙስሊሙ ያለውን ንቀት ትንሽም ለመደበቅ አለመፈለጉን በግልጽ አሳይቶናል፡፡ ይህ በምንም መልኩ በዝምታ የሚታለፍ አይደለም፡፡ የዛሬው የኢቴቪና የመንግስት ድርጊት እጅግ አሳዝኖናል፤ አሳፍሮናል፡፡ እንደ ሕዝብ መንግስት ነኝ ከሚል አካል የምንጠብቃቸው በርካታ በጎ ነገሮች ቢኖሩም በዚህ አይነት አሳፋሪ ስራ ውስጥ መንግስት ተጠምዶ ማየታችን ስለ አገራችን ዕጣ ፈንታ የምር እንድንጨነቅ ያደርገናል፡፡ የኛ ትግል ግን ነገም ከነገ ወዲያም ሚሊዮኖችን ከኋላው አስከትሎ ገና ይቀጥላል፡፡

 ትግላችን በወሬ እና በሀሜት የሚፈታ ቢሆን ኖሮ ድሮ እናየው ነበር፡፡ የኛ ትግል ግን በሰላማዊነትና በሕዝቦች የአብሮነት መተሳሰብና የሃይማኖት ቀናኢነት ላይ የተገነባ በመሆኑ እስከጥያቄያችን መመለስ ድረስ ይቀጥላል፡፡ ጥያቄዎቻችን ከማንኛውም የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብ የጸዱ፣ የሌሎችን እምነት እና መብት የማይጻረሩ ንጹሕ ሕገ መንግስታዊ የመብት ጥይቄዎች ናቸው፡፡ ኮሚቴዎቻችንም ሆነ ጥያቄዎቻችንን በየትኛውም መንገድ በመጠምዘዝ ከህዝብ ለማስጣል የሚደረገው ጥረት መቼም አይሳካም፡፡
በመጨረሻም ‹‹ፊልሙ›› ጠምዝዞና አወላግዶ የተለየ ውዥንብር ሊፈጥር ያደረገው ሙከራ፤ ሕዝቡ በሌላ አቅጣጫ መንግስት ሙስሊሙ ላይ እና ኮሚቴዎቹ ላይ የሚነዛው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ምን ያህል መሰረተ ቢስ እንደሆነ የተረዳበት ነው ብለን እንገምታለን፡፡ በተለይም የሌላ እምነት ተከታዮች በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይም ሆነ በሰላማዊ እንቅስቃሴው ላይ የተለየ አሉታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው የተደረገው ሙከራ እንደማይሳካ እንገምታለን፡፡ እኛም በነገው እለት ‹‹ፊልሙ›› ላነሳቸው ሃሳቦች ምላሽ የሚሰጥ የድምጽ ማብራሪያ ይዘን እንድምንቀርብ ቃል እንገባለን፡፡ በተለያዩ መንገዶችም ለሁሉም ለማዳረስ ዝግጅትና ጥረት እናድርግ፡፡
አላሁ አክበር

No comments:

Post a Comment