January 26, 2013 04:15
የላሊበላ ውቅር አብያተ ከርስቲያናት የመፍረስ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ መነገር የጀመረው ዛሬ አይደለም። ቢያንስ ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ያካባቢው ነዋሪዎች፣ በወፍ ዘራሽ ወደዚያ ያቀኑ ጋዜጠኞችና ለልቦናቸው የቀረቡ የገዳማቱ አገልጋዮች አስጠንቅቀዋል። ማስጠንቀቂያው ግዙፍና ዕረፍት የሚከለክል ቢሆንም ተግቶ ምላሽ የሰጠ አካል ባለመኖሩ፣ ጉዳዩን በመያዝ የተከራከረና ገዢውን ፓርቲ ያስጨነቀ የህዝብና የቅርስ ጠበቃ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ባለመገኘቱ “ለላሊበላ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች አንድ ናቸው” የሚል አስተያየት እየሰጡ ነው።
ዛሬ ጥያቄው አንድ ነው፡- “ለላሊበላ ማን ይድረስለት?” የሚል! የኢትዮጵያዊያን ጉልህ ታሪክ የሆነው ላሊበላ በመፍረስ አደጋ ውስጥ ነው፤ እየተሰነጣጠቀም ይገኛል፤ ውሃ ዘልቆት እየገባው ነው። ላሊበላ አንድ ቀን ወደ አለመኖር ሲቀየር “ሰበር ዜና” ማለትና ማላዘን ለማንም እንደማይጠቅም በአካባቢው የተገኙ የሚናገሩት ነው። ዜናውን የሰሙም የሚሰጡት አስተያየት ነው።
ሎንዶን እንደሚኖሩ ገልጸው ከሁለት ሳምንት በፊት በኢሜይል መልክት የላኩ አባት “ኢትዮጵያ ላሊበላን ያነጸውን ጠቢብና አሁን ያለውን ትውልድ እኩል ተሸክማ ትመግባለች” በማለት ራሳቸውንና የቀደመውን ጊዜ በማወዳደር ኮንነዋል። በርግጥም አዛውንቱ እንዳሉት በላሊበላ በርካታ ጸያፍ ተግባራት ስለመኖራቸው ይታወቃል።
ገዳማቱን በሚመሩት አስተዳዳሪዎች መካከል የሙስና ጦርነት አለ። ይህንኑ የሙስና ጦርነት በቅርቡ የጸረሙስና ኮሚሽን ሊመረምርና “ጀግንነቱን” ሊያሳይበት እንደሆነ ይነገራል። አዲስ አድማስ የተሰኘው የቀዳሚት ጋዜጣ በዓመት ከቱሪስት ብቻ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያለው የገዳሙ አስተዳደር፤ ብሩን እየዘረፈው እንደሆነ ጽፏል። ጋዜጣው ኖቬምበር 17/2012 ባሳተመው ዜና ሶስት ሆቴሎች፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ ለሁለገብ አገልግሎት የተከራየ ሶስት ህንጻ፣ ወፍጮ ቤቶችና ከሙዳዬ ምጽዋት ገቢ ቢያገኝም ገንዘቡ በጓሮ እየተዘረፈ መሆኑን አስታውቋል። የላሊበላ ውቅር አብየተክርስቲያናትን ታሪካዊ ዳራዎች ለመጎብኘት ከውጭ ከሚመጡ ቱሪስቶች ብቻ በዓመት ከ1.5ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ትርፍ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
ኦገስት 10/2011 ለንባብ የበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አንድ ውጪ አገር የሚኖሩ ያካባቢው ተወላጅ ለሚሌኒየም “ንግስ” አገራቸው ሄደው የታዘቡትን ሲገልጹ የላሊበላ ህዝብ መጸዳጃ ቤት የለውም ብለዋል። በያድባራቱ ጥጋ ጥግ ስለሚጸዳዱ ጠረኑ ጎብኚዎችንና ወደ አካባቢው ለሚመጡ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው የታዘቡትን ጽፈዋል። ከተለያየ ዓለም ይህንን ድንቅ ስፍራ ለመጎብኘት የሚመጡ፣ ላሊበላ እንኳን ሊጠገን የሰገራ ማስቀመጫ የተነፈገው ስፍራ መሆኑን በየጊዜው የሚታዘቡት ነው።
ጸሀፊው እንደጠቆሙት አቶ በረከትና የ“አማራ” ሊቀመንበር የሚባሉት አቶ አያሌው ጎበዜ በተወላጅነት ቡግና ወረዳ ተገኝተው የሚሌኒየም “ንግሱ” ላይ ከሕዝብ ጋር ተወያይተው ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ ከሰቆጣ፣ ከራያ፣ ከቆቦ፣ ከጎንደርና ከየጁ የሚዋሰነውን ላሊበላ በልማት እንዲያስቡት ተጠይቀው እነርሱም ቃል ገብተው ነበር። በተጨማሪም በአካባቢው ያለው የእርሻ መሬት ለምነቱን ያጣና ምርት የማይሰጥ የነጠፈ ስለሆነ የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ከገዳማቱ እንቅስቃሴ ጋር በመቆራኘቱ ለአካባቢው ልማት ትኩረት እንዲሰጥም ተማጽነው ነበር፡፡
አቶ በረከት በየት በኩል ቡግና እንደተወለዱና ተወላጅ ተብለው እነ ልደቱ አገር ሄደው “ቅሬታ ሰሚ” እንደሆኑ በውል ባይታወቅም የተጠየቁትን ለመፈጸም ቃል ገብተው ነበር። ጸሃፊው እንዳሉት በነበር ቀረ እንጂ። ሰሞኑን አዲስ ሆኖ የተነሳው የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት የመፍረስ አደጋ አቶ በረከት ቁብ ሊሰጣቸው እንደማይችል የሚያውቋቸው ሁሉ ይስማማሉ። አቶ አያሌው ጎበዜና እርሳቸው በበላይነት ለተካተቱበት ለ“ጭሰኛው” ብአዴን የላሊበላ ውድ ቅርሶች ከከርስ በላይ ሊሆኑ እንደማይችሉም ተመሳሳይ አቋም አለ።
ላለፉት አስርተ ዓመታት ስለ ላሊበላ ውድ ቅርሶችና የማምለኪያ አውዶች “የመውደም” አደጋ ሲነገረው የማይሰማው ህወሃት/ኢህአዴግ፣ ለአክሱም ታላቁ ቅርሳችን ከሰጠው ልዩ ትኩረት ሩቡን እንኳ ለላሊበላ አለመስጠቱ የስርዓቱ የጎሳና የብሄር ልክፍት ውጤት እንደሆነ የሚናገሩ ክፍሎች፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችንም ይወቅሳሉ። ለታሪካዊ ውድቀቱም ባለድርሻ ያደርጓቸዋል።
ላሊበላ ታላቁ ቅርሳችን አደጋ ላይ መሆኑ በይፋ ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ አንድም የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አቋም በመያዝ የማሳሰብ፣ ህዝብን የማስተባበር፣ የማሳወቅ፣ ለሌሎች ቅርሶቻችን እየተሰጠ ያለው ትኩረት ለላሊበላም እንዲሰጥ፣ ለቱሪዝም ንግድና ለዶላር መልቀሚያ ብቻ ሳይሆን ከምንም በላይ የሚጎላ የታሪክ ጉልላት መሆኑንን በማስታወቅ ገዢው ፓርቲ ሳይወድ በግዱ ችግሩ ሳይወሳሰብ ትኩረት እንዲሰጠው የማድረግ ስራ አልሰሩም በሚል ነው የሚተቹት።
በሳምንቱ መገባደጃ ሪፖርተር ለንባብ ያበቃውን ዜና ከሁለት ሳምንት በፊት ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ ኢቲቪን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወቃል። በወቅቱ የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክስርስቲያናት አደጋ ውስጥ መሆናቸውን፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህልና የመገናኛ ብዙሃን ቋሚ ኮሚቴ አባላት ትዝብታቸውን ማቅረባቸውን ጠቅሰን ነበር። ሪፖርተር የቅርስና ጥናት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታን በመጥቀስ እንዳለው ችግሩ የከርሰ ምድር ወይም የጂኦሎጂካል ነው። ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመቅረፍ ባገር ውስጥ ባለሙያ ስለማይቻል የተጎረደውን የአክሱም ሃውልት በማጋጠም የተከለው ድርጅት በመጋቢት ወር አገር ቤት በመግባት ጥናት አድርጎ መፍትሄ እንደሚፈልግ ነው የተናገሩት።
ከአስር ዓመት በፊት ለቀረበ ጥያቄና ከዚያ ቀደም ባለ ጊዜ ለተሰጠ ማስጠንቀቂያ ዝምታን የመረጠው መንግስት አሁን “ከተቻለ” በሚል ቀጠሮ የያዘው ለጥናት ነው። የራሱ የኢህአዴግ ሰዎች ግን “አስቸኳይ መፍትሄ ካልተፈለገ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሊፈርሱ ይችላሉ” በማለት እንቅጩን ተናግረዋል።
“የላሊበላ ሃውልት ለሌላው ምኑ ነው” አይነቱ “ሙት” አስተሳሰብ ካልያዛቸው በስተቀር በአክሱም ድንቅ የታሪክ አሻራችን መመለስ የተደሰትነውን ያህል ቢዘገይም ኢህአዴግ በተለይም ህወሃት ለላሊበላም እስካሁን ያባከነውን ጊዜ ሳይቆጥር ፈጥኖ በመድረስ ቢያንስ የአገር አስተዳዳሪነት ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባው ምክር የሚሰነዝሩ አሉ። እንዲህ ያለውን አኩሪና ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ተግባር ከማከናወን ይልቅ፣ ግለሰብና የግለሰብ አምልኮን አግዝፎ ታሪክን ለማዛነፍ የአገርና የህዝብ ገንዘብ ከመከስከስ በተሻለ፣ ይህንን ታላቅ የህዝብና የአገር ሃብት ለመታደግ እንዲተጋ የመወትወት ስራም እንዲሰራ ያሳስባሉ።
እነዚሁ ክፍሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የበጀትና የአየር ሰዓት ድጎማ እየተደረገለት ከመንደር አልፎ ብሔራዊ በዓል እንዲሆን ሌት ተቀን የሚደከምለትን የአሸንዳ በዓል ለማስተዋወቅ ከተሰጠው ትኩረት ጋር በማያያዝ የሚሉት አላቸው፡፡ “አሸንዳ ከጎጥና ከቀበሌ አልፎ ብሔራዊ በዓል ቢሆን ደንታ የለንም፡፡ ቄጠማ ለብሰው ሲጨፍሩ ለሚያያቸው ያስደስታሉ፤ በሽታ የሚሆነው ግን ላሊበላን የሚያክል ዓለም ያከበረውን ቅርስ እንደምናምንቴ ቸል ብሎ ዳንኪራውን ማስቀደሙ ላይ ነው” በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አያይዘውም የታሪክ ሽሚያ፣ የታሪክ የበላይነት፣ የኢኮኖሚ የበላይነት፣ የወንበር የበላይነት፣ የጠብመንጃ የበላይነት፣ የንግድ የበላይነት፣ የተስካር የበላይነት፣ … ከሁሉም በላይ ደግሞ ሌላውን ትውልድ ገባሪ የራሳቸውን ትውልድ አስገባሪ ለማድረግ ሌት ተቀን ሲደክሙ፣ ጭሰኞቹ የኢህአዴግ ፓርቲዎች የአራጋቢነት ሚና ተጫውተው ለማለፍ መወሰናቸው ነው፡፡
ጭሰኞቹ አዳማቂ ፓርቲዎች ከአገር ቅርስ ይልቅ ጥይት ላልተኮሱበት፣ ጅራፍ እንኳን ላልገመዱበት “ጀግንነታቸው” የሰማዕታት ሐውልት እያስገነቡ በምርቃቱ ውስኪ ይራጫሉ፡፡ ለግንባታው ከሚወጣው በመቶ ሚሊዮን ከሚቆጠር ብር ይዘርፋሉ፡፡ ለእነርሱ ላሊበላ ከከርስም ያነሰ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን የግሽበት ዘመን አዋቂዎቹ ክሸፈት እያሉ እየሰየሙት ነው፡፡ በምሬት አስተያየት የሚሰጡ “ብልጦቹ የወደፊት አስገባሪ ሲያዘጋጁ ከርሳሞቹ ግን ድንጋይ ጠፍጥፈው ሪባን በመቁረጥ የልጅ ልጃቸውን ለባርነት አሳልፈው ለመስጠት በግምገማ ይማማላሉ፡፡”
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አስራ አንድ ሲሆኑ የተሰሩበት ጥበብ አስገራሚነቱ አሁን ድረስ ለዓለም ግራ ነው። በ12ኛው ክፍለ ዘመን በጠቢቡ ንጉስ ላሊበላ የታነጹት ህንጻዎች በውስጣቸው አርባ መቅደሶች አሉዋቸው። “በመላዕክት እገዛ ታነጹ” የሚባሉት የጥበብ ቁንጮ መቅደሶችን የሚጎበኙ ሁሉ የዛሬው ትውልድ መጸዳጃ መስራት ተስኖት መመልከታቸው ያሳዝናቸዋል። እኛም ከማፈር ውጪ የምንለው ሊኖር አይችልም።
“በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በቅርስና ታሪክ ምርምር ላይ የሚሰሩ፣ የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለቤት ነን የሚሉ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ እንጠብቃለን በማለት የሚሰብኩ፣ አገራቸውን የሚወዱ በጠቅላላው ላሊበላ አፈ ታሪክ ከመሆኑ በፊት የሚጠበቅባቸውን ሊያደርጉ ግድ በሆነበት ወቅት ላይ ይገኛሉ። ላሊበላ ፈረሰ ማለት አገር ፈረሰ ነውና በፕሮጀክት፣ በስብሰባ፣ በድግስና በሴሚናር ገንዘብ ከመልቀም በላይ ትርጉም ያለው ተግባር ማከናወን የወቅቱ ጥሪ መሆኑንን የሚቃወሙ አይኖሩም። ይህ የማይመቻቸው የሙት መንፈስ አወዳሾችና የባርነት ገመዳቸውን በየቀኑ በራሳቸው ላይ የሚያጠብቁ ጭሰኞች ብቻ ናቸው” የሎንዶኑ ነዋሪ የኢሜል መልክት ነው።
ኢቲቪ ምስሉን ቆራርጦ ያሳየው ላሊበላ የመጨረሻው ደረጃ ላይ የመድረሱ ምልክት እየታየ ስለሆነ ከወዲሁ ጥበብ የተሞላበት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ልክ እንደ የአክሱም ሃውልት አስመላሽ ኮሚቴ አስቸኳይ ግብረ ሃይል በውጪና ባገር ቤት በማቋቋም አገራዊ ውለታ ማስቀመጥ አገር አፈራርሶና ያልፈነዳ ድማሚት ቀብሮ ከማለፍ እጅግ የሚሻል ወርቅ ተግባር ነውና ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለዚህ ተግባር አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ ታደርጋለች።
ዝግጅት ክፍሉ፤
No comments:
Post a Comment