Wednesday, 13 February 2013

ህግ ካልሰራ ጉልበት አማራጭ ይሆናል

 ከይኸነው አንተሁነኝ
የካቲት 13 2013


የሰው ልጅ ማህበራዊ ፍጡር ነው። ለመኖር በግል ከሚያስፈልጉት የምግብ፣ የአልባሳትና መኖሪያ ቤት ማሟላት በተጨማሪ ለቀን ከቀን እንቅስቃሴው እና አካባቢውን በተለየ መልኩ ለሱ እንዲመች አድርጎ ለማስዋብ ከሱ መሰል ሌሎች ሰዎች ጋር መተባበር የግድ ይለዋል። ሁሉንም ነገር በራሳችን የግል ጥንካሬና ችሎታ ብቻ መከወን ያለመቻላችን ሚስጥርም ጠፈጥሮአዊ ማህበራዊነታችን ነው። በእርግጥ ሌሎች እንሰሳትም በማህበር ይንቀሳቀሳሉ እንስሳዊ ፍላጎታቸውንም ያሟላሉ።

 እጅግ በጥልቀት በማሰብ ለምንቀሳቀሰው ለኛ ለሰዎች ግን ማህበራዊነት ከሁሉም በላይ ፋይዳው የገዘፈ ነው። ያንዳችን እንቅስቃሴ የሌላኛውን መንገድ እንዳያበላሸው ከሌሎች እንስሳት ይልቅ ቀርበን በመወያየት በመነጋገርና በመስማማት ለጋራ ጥቅም የጋራ ውሳኔ እናሳልፋለን። በዚህም መሰረት ትዳር ከመመስረት ጀምሮ ባካባቢያችን የምናቃቁማቸው እንደ እድር እቁብ፣ የሙያ ማህበራት፣ የደቦ ጊዜያዊ ትብብርና ሌሎችም መሰል ስብስቦች ያሉንን እለታዊ እንቅስቃሴዎች ለብቻችን ማሸነፍ ያለመቻላችን ችግር የፈጠራቸው ማህበራዊ መፍትሄዎች ናቸው።

እነዚህን ማህበራዊ ስብስቦች ለመምራት ደግሞ ህሊናዊ ዳኝነትን ከመጠቀም በተጨማሪ ሌሎችንም የጋራ ስምምነቶችንና መመሪያዎችን በስራ ላይ እናውላለን። ለሰው ልጅ ትልቁ ዳኛው የራሱ ህሊና ነው። ህሊናው የሚያዘውን ይከውናል። በግልም ሆነ በማህበር ለሚያጋጥሙት ችግሮች መፍትሄ የሚያገኘው ከህሊናው ሊሆን ይገባል።

 ነገር ግን ዓለም ሁሌም እነዲህ አይደለችም። አንዳንዱ የራሱን ጥቅምና ማንነት ከሌሎች በተለየ መልኩ ከፍ ለማድረግ፤ ባካባቢው የሚኖሩትን ሰዎች ፍላጎትና ጥቅም ለመጋፋት የራሱን ትልቅና ሀቀኛ ፍርድ ቤት ህሊናውን ይጨቁናል። “እየሰራህ ያለኸው ትክክል አይደለም” እያለ ሌት ከቀን የሚገስጸውን ህሊናውን በመጫን የሌሎችን ፍላጎት የሚጎዳ፣ የአካባቢ ሰላምና ማህበራዊ ግንኙነት የሚያደፈርስና የሀገርን ጥቅም የሚያጠፋ ስራ እንዳይሰራ በጋራና በሙሉ ስምምነት በጸደቀ ህግ ይገዛል።

 በዚህም መሰረት ለህሊናው ዳኝነት ያልተገዛ የማህበረሰቡ አባል በጋራ በተቀመጠው ህግ መሰረት አግባብነት ያለው ቅጣት እንዲቀበል ይደረጋል። ስለሆነም ማንኛውም የማህበረሰቡ አባል ይህ ህግ ሳይዛነፍና አንዱን በተለያ አቅርቦ ሌላውን ሳያርቅ፣ ላንዱ የበለጠ መብትና ጥቅም ሰጥቶ ለሌላው ሳያሳንስ፣ አንዱ የበለጠ እንዲተማመንበትና ሌላው ግን እንዲተራጠረው ሳያደርግ እንደሚሰራ እርግጠኛ ሊሆን ይገባል። በጥቅሉ ማንኛውም የማህበረሰቡ አባል ሁሉም ሰው ያለልዩነት በጋራ ለጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ ወይም ህግ እንደሚገዛ እርግጠኛ መሆን አለበት።

 ጠባብ ብሔርተኛው ድርጅት ወያኔና ጭፍን ተከታዮቹ ወያኔዎችስ ለዚህ የህሊና ዳኝነት በተለይም ለህግ የበላይነት ያላቸው አመለካከትና ክብር እስከ ምን ድረስ ነው? ወያኔዎች የነበረውን የዚያን ጊዜውን የህግ ስርአት ትክክል አይደለም፣ የሀገራችንን ሕዝብ በእኩልነት ለማስተዳደር ብቃት የለውም፣ በተለይ እጅግ ጠበው በመነሳት የኛ የሚሉትን የትግራይ ሕዝብ ይጨቁናል በማለት የሃይል አማራጭን እንደተከተሉ ሁሉ፤ አሁንስ ተመሳሳይ ምክንያቶችን በማንሳት የሃይል አማራጭን ለመከተል ለወሰነ ሕዝብ መላሻቸው ምንድን ነው?…

ወያኔ ጠንካሮችን ለማንበርከክ፣ ያልነበረውን እንዳለ የነበረውንም እንዳሌለ ለማስመሰል፣ ያገዛዝ ስርአቱን መልካም አስመስሎ ለማሳየት ወይም ያልፈለጋቸውን እሱ በፈለገው ምልክ ለማቅረብ በቀጥታ ሃይል ከመጠቀም አንስቶ መረጃ መዝረፍ፣ ማጥፋትና ማቃጠልን ጨምሮ የሃሰት ምስክሮችን እስከማቅረብና በጣም ሲከፋ ደግሞ ሁሌም ሲያደርገው እንደነበረውና ሰሞኑንም እንደደገመው በውሸት የተቀነባበሩ ፊልሞችን በማዘጋጀት የግልም ሆነ የጋራ መብታችንን ሲረገጥ መቆየቱ አሌ የሚባል አይደለም።

ሙስሊምና ክርስቲያን ማሕበረሰቦችን በማጋጨት ከሁለቱም በኩል የተለየ ድጋፍን ለማግኘት በማስላትና የአገዛዘዝ ዘመኑን ለማራዘም አስቦ ከሰራው ጅሃዳዊ ሀረካት ከተሰኘው የወረደ የፊልም ቅንብር በፊትም ወያኔ ሌሎች ቅንብሮችን አዘጋጅቶ ማስመረቁ የሚዘነጋ አይደለም። ከዚህ በፊትም በ2003 ዓ/ም መጠናቀቂያና 2004 ዓ/ም መግቢያ አካባቢ ወያኔ ከግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ጋር ግንኙነት አላችሁ ባላቸው ብዙ ኢትዮጵያዊያን ላይ ተመሳሳይና የወረደ የፊልም ቅንብር ሰርቶባቸዋል። አግባብነት የሌለው ፍርድም እንዳሳለፈ የቅርብ ጊዜ የሃዘን ትዝታችን ነው።

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ላይም በተደጋጋሚ ተመሳሳይነት ያለቸውና አልፎ አልፎም ድርጅቱ ሰብአዊ ርህራሄ የጎደላቸው እኩይ ተጋባራትን እንደፈጸመ በማስመሰልና ፊልሞችን በማቀነባበር አቅርቧል። ጥቅም አገኘበታለሁ ብሎ እስካሰበ ድረስ ማንኛውንም ነገር ከመከወን የማይመለሰው ወያኔ፤ በተደጋጋሚና በተለያዩ ቦታዎችና ወቅቶች ፈንጂዎችንና ቦንቦችን እራሱ በማፈንዳትና ምንም የማያውቁ ንጹሃን ኢትዮጵያዊያንን በጅምላ በመፈጀት፣ ህንጻዎችንና ድልድዮችን በራሱ መንገድ በማፈራረስ ኦነግ እንደፈጸመው በማስመሰል የሃሰት የፊልም ቅንብር አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አቅርቧል። ይህ እኩይ ስራው በዊክሊክስ አማካኝነት ቢጋለጥበትም አሁንም የውርደት ስራውን እንዳላቋረጠ ጅሃዳዊ ሃረካት ከተሰኘው የሰሞኑ የፊልም ቅንብር እንረዳለን።

የወያኔ የፊልም ቅንብርና ዝግጅት አመል ከኢትዮጵያዊያን አልፎ በስዊድን ጋዜጠኞች ላይም ተተግብሯል። በሃይል የተባሉትን እንዲሉና በርሃ ላይ እየተሯሯጡ የተጠኑ ትዕይንቶችን እንዲተውኑ ተደርገዋል። ይህም ተቀነባብሮና ተስተካክሎ ሁላችንም እንደምናስታውሰው ለፍርድ ቤት በማስረጃነት ቀርቦ አስቀጠቷቸዋል። እንደግዲህ ከዚህ ሁሉ የመንረዳው ወያኔ አስቸገሩኝ የሚላቸውን ግለሰቦች፣ ማህበራት፣ ድርጅቶችና የማሕበረሰብ ክፍሎች ለማንበርከክና ማንኛውንም ፖለቲካዊም ሆነ ማሕበራዊ ኩነት እሱ በፈለገው መልኩ ባቻ ለማስኬድ የውሸት ፊልም ቀረጻ ድረስ የደረሰ ስራና ከዚህም በላይ እንደሚሰራ ነው።

ጅሃዳዊ ሃረካትና ይህን የመሳሰሉ የወያኔ የቀደሙ ስራዎች ህግ ተብሎ የተቀመጠውን የወያኔ የይስሙላ ህግ እንኳ አጣሞ ለመተርጎም ሆን ተብለው የተሰሩ ስራዎች ናቸው። በተለይ ሰሞኑን ይህ ጅሃዳዊ ሃረካት ፊልም እንዳይታይ በዚሁ ህግ ቢታገድም እግድ ተጥሶ እንዲታይ መደረጉ ይህ ህግ የተባለው የወያኔ የይስሙላ ህግ እንኳ በቅጡ እንዳይሰራ ጉልበተኞች ሊያቆሙት መቻላቸውን ያሳያል።

 ስለዚህ ይህ የይስሙላ ህግ እንኳ ለተወሰኑት የሚሰራ ለተቀሩት ደግሞ በወረቀት ላይ የሚነበብ ሆኗል ማለት ነው። ታዲያ በተግባር ይህ ከሆነ እንግዲህ ህግን አምነው በህግ ብቻ ተማምነው ለሚኖሩ ምን ቀረላቸው? ይህ የተወለካከፈ ህግ ተብየ ህግ አንደማይሰራ የተረዳው ማሕበረሰብስ የሚወስደው እርምጃ ምን ሊሆን ያችላል? በህግ ስርአቱ ተስፋ የቆረጠ ሕዝብስ መብቱን በጉልበቱ ለማስከበር ቢንቀሳቀስ ወንጀል ነው የሚለው ማነው? መልሱን ላድማጭ ትቸዋለሁ። አበቃሁ።

No comments:

Post a Comment