ኤፍሬም እሸቴ
በንግግርም ይሁን በጽሑፍ ለማንሣትም ሆነ ለመጥቀስ፣ ለመወያየትም ሆነ ለመከራከር ከማይመቹኝ (discomfort እንዲል ፈረንጅ) የኢትዮጵያ ርዕሰ ጉዳዮች ሁሉ ዘርን፣ ብሔረሰብን የተመለከተው ዋነኛውና አንዱ ነው። ጉዳዩ በዕለት ተዕለት የአገራችን ሕይወት ውስጥ ወሳኙ እና በሁነኛ መልክ ማኅበረሰባዊ ማንነታችንን እየበየነ እንዳለ እያወቅኹም እንዲህ እንደ አሁኑ በአደባባይ ለመውጣት ግን ብዙም አይቀለኝም። ምክንያቱ ሌላ ምንም ሳይሆን ጉዳዩ ያለው ስሱነት (sensitivity) ነው። አሁን ግን ላልፈው አልቻልኩም። አይገባምም። ለምን?
መነሻ
ከአማራ ክልል ወደ ቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ ተጉዘው የከተሙ በርካታ ሰዎች በወረዳው ባለሥልጣናትና ፖሊሶች፤ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የሚያትት ዜና የሰሞኑ ኢትዮጵያውያን ድረ ገጾች/መገናኛዎች ዋነኛ ትኩረት ነው። ስለዚሁ ጉዳይ ዜና ያስነበበው “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ጉዳዩን በተመለከተ የሚከተሉትን ቁም ነገሮች አስፍሯል።
- በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ቦታ በማጣታቸውና የተሻለ ሥራ ፍለጋ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ መሔዳቸውን፣
- “ከሌላ ቦታ እየመጣችሁና እየሠራችሁ የአካባቢውን ተወላጅ ሰነፍ አደረጋችሁት” በሚል ምክንያት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ሳይሰበስቡ ከክልሉ እንዲወጡ መደረጋቸውን፣
- አንዳንዶቹ በያሶ ወረዳ ውስጥ የከተማ ነዋሪነትና የንግድ ፈቃድ በማውጣት ላለፉት ሰባት ዓመታት በሥራ ላይ መቆየታቸውን፣ ገሚሶቹ ደግሞ ከ1997 ጀምሮ የቀበሌው ነዋሪ በመሆን ከክልሉ ተወላጆች ጋር በስምምነት መሬት የእኩል እያረሱ የራሳቸውንም የባለመሬቱንም ሕይወት መቀየራቸውን፣
- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይ ዞን በያሶ ወረዳ ውስጥ በሀሎ ትክሻ፣ ሆኒ፣ ሊጐ፣ ባብርኮ፣ ሻብቲ፣ ድልድል፣ ቲኒጆ መጢና በመሰል ቀበሌዎች በግምት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ ከአማራ ክልል የመጡ ሰዎች እንደሚገኙበት፣
- “የክልሉ ነዋሪ ወዶንና ተቀብሎን በሰላም ነበር የምንኖረው” ማለታቸውን፣
- ጐጐታ በተባለ ቀበሌ ከአማራ ክልል የመጡ 43 ሰዎች እንዲሁም በሀሎ ሙከአርባ ቀበሌ የ25 ሰዎች መታወቂያ ተቀዳዶ ሲጣል መመልከታቸውን፣
- “እስከአሁን በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ከታሠሩት በርካታ ሰዎች በተጨማሪ በመኪና ተጭነው ነቀምትና ጊንቢ የተወሰዱት ሰዎች” መኖራቸውን፤ ስንቅ ሊያቀብሉ የሔዱ ሰዎችም መታሰራቸውን፤
- ወደመጡበት እንዲመለሱ የተወሰነው፤ በብአዴን፣ ኦህዴድ እና የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ በኾነው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ ፓርቲ (ቤጉብዴፓ) በጋራ ተወያይተው በደረሱበት ውሳኔ መኾኑን ሥራው የወረዳው ብቻ ሳይሆን ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በትስስር እየተሠራ መኾኑን የያሶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ሻምበል ዳኛ መግለጻቸውን ዘግቧል።
ሊወገዝ የሚገባው ተግባር
መነሻው ምንም ይሁን ምን፣ የክልሉ ፓርቲ ከማንም ጋር ይስማማ አይስማማ በነዚህ ዜጎች ላይ የተደረገው ተገቢነት የሌለው ነገር ነው። የዜጎች በአገራቸው ውስጥ የመዘዋወር፣ የመኖር መብት እንዲህ በጥቂት የፓርቲ ሹመኞች መወሰኑ የሚያስጨንቅም የሚያስደነግጥም ምልክት ነው። ከጉራ ፈርዳም ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉት ሰዎች “አማሮች” መሆናቸው ደግሞ አጋጣሚ ነው ለማለት በጣም የዋህ (ሲገፋም ጅል) መሆን ይጠይቃል።አማራ” የሚባል ለብዙዎቹ “ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” ጠላት የሆነ አካል እንዳለ በጓዳም በአደባባይም ሲነገር ብዙ ጊዜ ሰምተናል። ይህ ‘ፖለቲካ ያባውን – መፈናቀል ቢያወጣው’ (ሆድ ያባውን … እንደሚባለው) ምንጩ የማይታወቅ የማይሆነውም ለዚህ ነው።
ከደቡብም ከቤንሻንጉልም ለመፈናቀል “አማራነቱ” ምክንያት የሚሆንበት ከሆነ “አይቴ ብሔሩ ለአማራ? … የአማራ አገሩ የት ነው?” የትስ ሔዶ ይኑር? ኢትዮጵያ አገሩ አይደለምን?” ለማለት ያስገድደኛል። ደግሞስ አንድ ሰው አማርኛ ስለተናገረ የግድ ወደ አማራ ክልል መሔድ አለበት? ሁሉም ወደየክልሉ የሚለውን አዋጅ ያወጣውስ ማን ነው? አማርኛ የሚናገሩ ነገር ግን “የአማራ ክልል አገራቸው ያልሆኑ” ኢትዮጵያውያን የነገ ዕጣ ፈንታ ምንድር ነው?
የመታወቂያ ነገር
ለረዥም ጊዜ የቀበሌ መታወቂያ ሳይኖረኝ እኖር ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን የግድ የቀበሌ መታወቂያ ማውጣት የሚያስፈልገኝ ጊዜ ደረሰና እኖርበት ወደነበረው ቀበሌ ሔድኩ። ፎርም ሞላኹ። ከዚያም መታወቂያው ላይ መስፈር ያለበት የብሔረሰብ (እነርሱ እንኳን ብሔር ነው ያሉት) ነገር ተነሣ። መናገር አልፈለኩም። ቀበልዬው ካልተናገርኩ እንደማይሰጠኝ እርግጥ አደረገው። መሞላት አለበት። የዘር ማንዘሬን “ደም” ሁሉ እስኪሰለቸው ደረደርኩለት። በምን ፎርሙላ እንደሆነ ባላውቅም እርሱ ደስ ያለውን አንዱን ቋንቋ ብቻ መርጦ ብሔሬን ሞላው። በመታወቂያዬ መሠረት ቀብልዬው የሞላው ክልልና ብሔር አባል ሆንኩ። መታወቂያ እየታየ ሰልፍ መያዝ ሲጀመር እኔም አቶ ቀበልዬው በሞላው ተርታ የግዴን ልገባ ነው ማለት ነው።
ማንነትን በማወቅ ሰበብ ማንነትን ማጣት
ማንነትን ማወቅ፣ ባህልን መጠንቀቅ፣ ቋንቋን ጠብቆ መቆየት የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን መብትም ነው። ነገር ግን አሁን ባለው መንገድ ድንበር እያጠሩ ሰውን ያለ ፍላጎቱ “ሰልፍህ በየት በኩል ነው?” የሚያስብል ብሔረሰባዊ አሰላለፍ ግን ጤናማ ካለመሆኑም በላይ አገር ብለን በጋራ የምንኖርባትን ጎጆ የሚያፈርስ ከፋፋይ አስተሳሰብ ነው። በተለይ እዚህ አሜሪካን አገር ከመጣኹ በኋላ ያየሁት እና እንኳን ቋንቋን ቀለምን ማለትም ነጭ፣ ጥቁር፣ እስያዊ፣ ሂስፓኒክ የሚለውን እንኳን ፎርም ላይ ለመሙላት የሰውየው ብቸኛ ፍላጎት መሆኑን ማወቄ በግዳቸው “ብሔረሰብ እንዲመርጡ” ለሚደረጉ ኢትዮጵያውያን እንዳዝንም፣ እንድቆጭም፣ እንድበሳጭም ያደርገኛል።
ዛሬ አማራ ተብለው እንዲወጡ የተደረጉት ዜጎች ሌላው ሰው “አማራ” ይላቸው ካልሆነ ምናልባት ራሳቸውን በቀበሌያቸውና በትውልድ ቀዬያቸው ከመጥራት የዘለለ ነገር የሚኖራቸው አይመስለኝም። እንዳሁኑ “አማራ ናችሁ” የሚለው አንድ ቃል ሳይጫንባቸው በፊት “አገራችን ጎጃም ነው” ወይም “መንዝ ነው” ይሉ ይሆናል። ኦሮሞውም “ሜታ ነኝ” ወይም “ቦረና ነኝ፣ ወለጋ ነኝ” ይል እንደሁ እንጂ እንደአሁኑ “ኦሮሞነት” አልተጫነበትም ነበር። ሌላውም ሌላውም። ማንነትህን እወቅ በማለት ሰበብ የተጫነበት የቋንቋ ቀንበር ከጎረቤቱ የሚለየውና አርሶ ከሚያድርበት ቀዬ የሚያፈናቅለው ከሆነ ማንነቱ እንደ ዕዳ ተቆጥሮበታል ማለት ነው።
ሌላው የሚያስጨንቀው ጉዳይ ምንነትን በማጠር ሰበብ ክፉ የፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱ ቡድኖች መኖራቸው ነው። የዚህ ጨዋታ ግንባር ቀደሙ ደግሞ ኢሕአዴግ ራሱ መሆኑን መናገር አገራዊ ግዴታ እየሆነ ነው። ፓርቲው ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም አገርን የሚያክል ትልቅ ቤት የሚያፈርስ ቁማር ውስጥ ነው ያለው። የሌሎች ብሔረሰቦችን ድጋፍ ለማግኘት አማራውን የመስዋዕት በግ አድርጎ የማቅረብ ቁማር። ዞሮ ተመልሶ ወደራስ ሊተኮስ (Backfire ሊያደርግ) የሚችል መድፍ መጫወቻ ማድረግ።
መረጫጨት ተጀመረ?
አንድ ሰሞን ዝነኛ የነበረች ቀልድ “መረጫጨት ተጀመረ” ትል ነበር። የንስሐ አባት ጸበል ሲረጩ ለጨዋታ የመሰለው ትንሽ ነካ ያደረገው ሰው “መረጫጨት ተጀመረ?” ብሎ ውኃ ያነሳበት ታሪክ። በዚህ ዓይነቱ ከባድ ርዕስ ላይ ይኼ ቀልድ ስላቅ ሆኖ በውስጤ ብቅ አለ። ዛሬ ያባረሩ ሰዎች በሌላው ዘንድ “መረጫጨት ተጀመረ?” እንደማያሰኝባቸው ማወቅ ተስኗቸው ነውን? ምናልባትም ይህ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው ማን ያውቃል። እንደመንደር ጎረምሳ “ሰፈሬ ለምን መጣህ?” ሲሉ ሌላው በተራው እነርሱን “ሰፈሬ ለምን መጣችሁ?” እንዲላቸው ፈልገዋል ማለት ነው? ከዚያስ? ተጠቃሚው ማን ሊሆን? ወይስ ካርዱን የሚጫወተው ዋናው ሰውዬ ከኋላ ሆኖ እንዲስቅ? ኢትዮጵያችን እንደማትጠቀም በርግጠኝነት መናገር እችላለኹ።
ለጊዜው
በእኔ ትንሽ ግምገማ ኢትዮጵያውያን በመታወቂያቸው እና በስማቸው እየተገማመቱ እንዲደባደቡ ትልቅ ፍላጎት አለ። እስካሁን ፍላጎቱ ያልተሳካው በኢትዮጵያውያን አርቆ አሳቢነት ነው። ይህንን የኢትዮጵያውያን አርቆ አሳቢነት በሕይወቱ ያልተረዳ እና በዚህ የዘር ፖለቲካ የተጠመቀ ትውልድ አገሪቱን እየተረከበ ሲመጣ እንዴት እንደምንሆን ግን እግዜር ይወቀው። ባለ ራእዩ ሰውዬ “አንተርሐሙዌ” (Interahamwe) ብለው ያሟረቱት ነገር ላለመድረሱ ማረጋገጫ የሚሰጥ ባገኘኹ በተደሰትኩ።
የቤንሻንጉል ክልል ሰዎችም ሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለዚህ ዕብደት አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት አለባቸው። በዚህ ነገር መጠየቅ ሲመጣ ማዕከላዊው መንግሥትም “አልነበርኩበትም፣ የክልሉ ጉዳይ ነው” ማለት አይችልም። መሬት ለሕንዶች በነጻ በማከፋፈሉ ላይ እጁን የሚያስገባው የቤተ መንግሥት አካል ድሃ ገበሬዎች ሲፈናቀሉ የለኹበትም ሊለን አይችልም። የሚሰማውም አያገኝ።
መቼም የእምነት መሪዎቻችን ራሳቸውን ችለው ቆመው “ተዉ” ይላሉ ብለን አንጠብቃቸውም። እንዲህ ዓይነቱ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲገታ መጠየቅ የሚገባቸው እነርሱ ቢሆኑም – በቅድሚያ። እነርሱ ባይናገሩም ሥልጣን ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ሐሳባቸውን መግለጽ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ነገሩ ወንጀል መሆኑን መናገር አለባቸው። “ትክክል አይደለም” ለማለት የግድ የአማራነት ቆብ መድፋት አያስፈልገንም። ሰብዓዊነት የሚሰማው በሙሉ ግድ ይለዋል። ለታሪክም ቢሆን።
ከጊዜያዊ የፖለቲካ ወገንተኝነት ውጪ ማሰብ የሚያስፈልገው በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ነው። የገዢው ፓርቲ ደጋፊና መሪ የሆኑትም ቢሆኑ ይህንን መቃወም ኢሕአዴግን መቃወም አድርገው መቁጠር አይገባቸውም። እንዲያውም ያስመሰግናቸዋል። ለኅሊናችንና ለልጅ ልጆቻችን ስለምናስረክባት ኢትዮጵያ ስንል “ኧረ በሕግ አምላክ፣ ኧረ በባንዲራው” እንበል።
No comments:
Post a Comment